የአንድን ድርጅት ትክክለኛ የገበያ ዋጋ ማወቅ፡ ለንግድ ስኬት ወሳኝ መደላድል ነው። የቢዝነስ ቫሉኤሽን ማለት ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ያለውን አጠቃላይ የገበያ ዋጋ በሳይንሳዊ መንገድ የመተመን ሂደት ነው። በአሁኑ ወቅት የሀገራችን የንግድ ሥነ-ምህዳር በአዲሱ የንግድ ሕግ እና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎች (IFRS) እየተቀረጸ ባለበት ወቅት፣ የቢዝነስዎን ዋጋ አለማወቅ ትልቅ የስትራቴጂክ ስህተት ሊሆን ይችላል።
በኢትዮጵያ ሁኔታ አብዛኞቹ የቢዝነስ ባለቤቶች ትኩረት የሚያደርጉት በሚጨበጡ ንብረቶች (Tangible Assets) ላይ ነው። እነዚህም የሊዝ መብት፣ ሕንፃዎች፣ ማሽነሪዎች እና የመጋዘን ክምችቶችን ያካትታሉ። እነዚህ ንብረቶች ለባንክ ብድር ዋስትና እና ለድርጅቱ መረጋጋት መሠረት ቢሆኑም፣ የቢዝነሱን ሙሉ አቅም ግን አይገልጹም። እውነተኛው የድርጅት ጥንካሬ የሚመነጨው በዓይን ከማይታዩ ነገር ግን ከፍተኛ ገቢ ከሚያስገኙ የማይጨበጡ ንብረቶች (Intangible Assets) ጭምር ነው።
የማይጨበጡ ንብረቶች የሚባሉት እንደ ድርጅቱ መልካም ስም (Goodwill)፣ የንግድ ምልክት (Trademark) ፣ የታማኝ ደንበኞች መረጃ (Customer Bases) እና እነዚህን የመሳሰሉት ከዕውቀትና ከንግድ ግንኙነት ጋር የሚገናኙ ንብረቶች ናቸው። ብዙ ጊዜ በሀገራችን እነዚህ እሴቶች ሳይገመቱ ይቀራሉ። ነገር ግን ድርጅትን ለመሸጥ፣ አዲስ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ወይም የባለቤቶችን ድርሻ ለመወሰን እነዚህ የማይጨበጡ ንብረቶች ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ።
ስለሆነም፣ የቢዝነስዎን ዋጋ በባለሙያ በማስገመት የድርጅትዎን ተወዳዳሪነትና ትክክለኛ ደረጃ እንዲያውቁ ይመከራል።



Leave a Reply